የሀገር ውስጥ ዜና

513 የኢነርጂ ዘርፍ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ወስደዋል- ባለስልጣኑ

By amele Demisew

January 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ለ513 የኢነርጂ ዘርፍ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ መስጠቱን የነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን ገለጸ ፡፡

በኤሌክትሮ መካኒካል እና በኤሌክትሪካል ሥራ ተቋራጮች እንዲሁም በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የማማከር አገልግሎት የብቃት ማረጋገጫ እየተሰጠ መሆኑን በባለስልጣኑ የኢነርጅ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ዴስክ ኃላፊ ቀለሙ ታመነ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በ2016 በጀት ዓመት ለ326 ተቋማት እና በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ ለ187 ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ መሰጠቱን  ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሮ መካኒካል ኢንጂነሪንግ  የማማከር አገልግሎት የብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት መመሪያው እየተከለሰ ስለመሆኑም  አንስተዋል ፡፡

በኢነርጂ ዘርፍ ባሉ አካላት የሚና መደበላለቅ መኖሩን ጠቁመው÷ ያለዘርፋቸው ሲሠሩ በተገኙ ተቋማት ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ እስራት የሚደርስ ርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

ባለስልጣኑ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ አገልግሎቱን በኦንላይን እየሰጠ ቢሆንም÷ ከተገልጋዮች በኩል ግን የተሳሳተ መረጃ የማስገባት፣ የማይገባቸው ቦታ ላይ የመሙላት እና መሰል ችግሮች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ