የሀገር ውስጥ ዜና

ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያለኝን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ነኝ አለች

By amele Demisew

January 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልፃለች፡፡

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ከጣሊያን የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ሚኒስትር አና ማሪያ በርኒኒ ጋር በኢትዮጵያን ዲጂታል ለውጥ እና በፈጠራ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እድገትን በማጠናከር ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ በለጠ ሞላ(ዶ/ር)÷የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂና ፈጠራ ተግዳሮቶችን በመፍታት እና ቴክኖሎጂን ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት በማዋል ረገድ ምቹ ስነምህዳርን ለመፍጠር የትብብር አስፈላጊነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጣሊያን የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ሚኒስትር አና ማሪያ በርኒኒ በበኩላቸው÷ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀው፤ የዲጂታል ፈጠራ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት ያለውን የለውጥ አቅም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፣ በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ፣ በኒኩለር ሳይንስ እና በምርምር ዘርፍ ጣሊያን በትኩረት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባም ማንሳታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሁለቱ ሚኒስትሮች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ያለመ የትምህርት ልውውጥ መርሃ ግብሮችን እና የጋራ የምርምር ስራዎችን ጨምሮ የወደፊት የትብብር መስኮች ላይም መክረዋል።