የሀገር ውስጥ ዜና

የኮምቦልቻ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል ተባለ

By amele Demisew

January 30, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ ከ515 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በዚህ አመት ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በቦታው ተገኝተው የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

በጉብኝቱ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ኢ/ር)÷ ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል::

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት በአግባቡ እየተከናወነ በመሆኑ በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለከተማው ህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ዘላቂ እና አስተማማኝ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ይሆናል ብለዋል።

250 ሺህ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርገው ፕሮጀክቱ፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ የከተማውን የውሃ ሽፋን ከነበረበት 61 በመቶ ወደ 100 በ መቶ ከፍ ያደርገዋልም ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ አምስት ጥልቅ ጉድጓዶች ያሉት ሲሆን በአጠቃላይ በሰከንድ 250 ሊትር ውሃ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚገመት ተገልጿል።

700 ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው የማጠራቀሚያ ጋንና 5 ሺህ ሜትር ኩብ የመግፋት አቅም ያለው ግፊት ጣቢያም ተሠርቶለታል።