አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱ ተገለጸ።
በክልሉ የ6 ወራት የስራ አፈፃፀምና የፓርቲ ስራዎች የገምገማ መድረክ ላይ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰለሞን በቀለ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት በክልል የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 54 ባለሀብቶች ፍቃድ መሠጠቱን ገልፀዋል።
ፈቃድ የተሰጠውም በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን ጠቁመው፣ ለኢንቨስትመንት የሚሆን 7 ሺህ 635 ሄክታር መሬት የመለየት ስራ መሠራቱንም ተናግረዋል።
ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አኳያ ባለሀብቶችን በማስተባበር 55 ኪሎ ሜትር የመዳረሻ መንገድ ግንባታ ማካሄድ እንደተቻለም ጠቁመዋል።
በነዚህ ወራት በክልሉ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች 10 ሺህ 435 ሄክታር መሬት ማስተላለፍ መቻሉንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከዚህ ቀደም የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ 70 ድርጅቶች ላይ የመሬት ኦዲት በማድረግ ወደ ስራ ያልገቡ 10 ሺህ 295 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጉንም በሪፖርታቸው አንስተዋል።