የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የኮሪደር ልማት በርካታ  የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮች ተገነቡ

By Meseret Awoke

February 06, 2025

አዲስ አባ፣ ጥር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በመዲናዋ በተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በርካታ የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮች መገንባታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ነጻነት ዳባ እንዳሉት ፥ ኮርፖሬሽኑ በመንግስትና በተለያዩ ተቋማት አማካኝነት የለሙ የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮችን ተርክቦ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ እየሰራ ነው፡፡

የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮችን በመከታተል ለህብረተሰቡ ምቹ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግም የተለያዩ ሥራዎች በመሥራት ላይ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በመዲናዋ የተገነቡና በመገንባት ላይ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው ፥ ኮርፖሬሽኑ እስከአሁን ተገንብተው የተጠናቀቁ 27 የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን መረከቡን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ፣ የማልማትና ነባሮቹንም የማደስ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዘርፉ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ፥ በግማሽ ዓመቱ በኮሪደር ልማት የተገነቡ የህዝብ መዝናኛዎችን ሳይጨምር ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎች የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችን መጎብኘታቸውንም ተናግረዋል።

በኮርፓሬሽኑ ስር የሚገኙ የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮች አገልግሎት በአብዛኛው በነጻ መሆኑንና በውስን ፓርኮች ላይ ለተለያዩ አገልግሎቶች መሸፈኛ ሲባል አነስተኛ ገቢ እንደሚሰበሰብ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በግማሽ ዓመቱ 60 ሚሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉንና ከአምስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፈጠሩን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡