የሀገር ውስጥ ዜና

ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የተጀመሩ ጥረቶች አበረታች ናቸው-ከንቲባ ከድር ጁሃር

By amele Demisew

February 06, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የተጀመሩ ጥረቶች አበረታች መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት በ3ኛ የስራ ዘመን 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባዔ የከተማ አስተዳደሩ የመጀመሪያው ስድስት ወር የአስፈጻሚ እና ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል ፡፡

ከንቲባ ከድር ጁሃር በዚህ ወቅት÷በአስተዳደሩ ባለፉት ስድስት ወራት በገቢ አሰባሰብ፣ በገበያ ዋጋ ማረጋጋት እንዲሁም ስራ ዕድል ፈጠራ ረገድ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ በመጀመሪያ ስድስት ወራት ከያዘው ዕቅድ 94 በመቶ ማሳካት መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡

በዚህም በስድስት ወር ውስጥ ለ10 ሺህ 588 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ9 ሺህ 995 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም የሥራ አጥነት ምጣኔን ከ18 ከመቶ በታች ለማድረስ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት እንደተቻለ መገለጹን የከተማው ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡