ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሜክሲኮ 10 ሺህ ወታደሮቿን በአሜሪካ አዋሳኝ ድንበር ላይ አሰማራች

By Mikias Ayele

February 06, 2025

አዲስ አባ፣ ጥር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ዛቻን ተከትሎ ሜክሲኮ 10 ሺህ ወታደሮችን በዩናይትድ ስቴትስ አዋሳኝ ድንበር ላይ ማሰማራቷን አስታወቀች፡፡

የሜክሲኮ ፕሬዚዳንት ክላውዲያ ሼንቦም ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተክትሎ የሀገሪቱ ብሄራዊ ጦር አባላት ከአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ጋር በሚዋሰኑት ሱዳድ ጁዋሬዝና ኢል ፓሶ በተሰኙ አካባቢዎች መስፈራቸው ተገልጿል፡፡

ዛሬ ጠዋት ላይም ጭንበል የለበሱና የታጠቁ ከ1 ሺህ 650 በላይ የሜክሲኮ ብሄራዊ ጦር አባላት በድንብር አካባቢ በመስፈር በአካባቢው ቅኝት ሲያደርጉ መታየታቸው ነው የተገለጸው፡፡

ሜክሲኮ ወታደሮቿን ለማስፈር የወሰነችው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሜክሲኮ ምርቶች ላይ ከበደ ያለ ታሪፍ እንደሚጥሉ መናገራቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

ወታደሮቹ በዋናነት በሜክሲኮ እና አሜሪካ ድንበር የሚደረጉ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚቆጣጠሩ ሲሆን÷ በተጓዳኝ ከአሜሪካ መንግስት የሚሰነዘርባቸውን ማንኛውም ጫና ለመመከት እንደሚሰሩ መጠቀሱን ቲ አር ቲ ዘግቧል፡፡

ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት በተመለሱበት ማግስት ከሜክሲኮ ሕገ-ወጥ ስደተኞች ወደ አሜሪካ ይገባሉ በሚል ሜክሲኮን ሲከሱ የቆዩ ሲሆን÷በሜክሲኮና አሜሪካ ድንበር ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸውም ይታወሳል፡፡