አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋይዳ የዜጎችን መብት የሚያስጠብቅ፣ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅም የሚያስከብር መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ም/አስተባባሪ ራሄል ይትባረክ ገለጹ።
አስተባባሪዋ “ፋይዳ ለኢትዮጵያ” በሚል እየተካሄደ በሚገኘው የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት÷ፋይዳ የዜጎችን መብት የሚያስጠብቅ፣ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅም የሚያስከብር ነው፡፡
በኢትዮጵያ የነዋሪዎችን የመታወቅ መብት ለማረጋገጥ፣ በአገልግሎት ሰጪና ተቀባዮች መካከል መተማመን እንዲዳብር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግልጽነት ተጠያቂነትና የተሳለጠ አሰራር ስርዓት ለመፍጠር የዲጂታል መታወቂያ ገቢራዊ መደረጉንም ነው የገለጹት።
ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ እንደ ስሙ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የጎላ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው የዜጎችን መብት የሚያስጠብቅ፣ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅም የሚያስከብር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ በአዋጅ ቁጥር1284/2015 ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባ ሲሆን እስካሁን ከ12 ሚሊየን ያህል ነዋሪዎች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት መሆናቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በአዲስ አበባ በርካታ ነዋሪ መመዝገቡን አንስተው በክልሎች ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።