አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ የወባ በሽታ ስርጭትን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ÷በወረርሽኝና በወባ ምክንያት የሚፈጠር ስቃይን ብሎም ሞትን ለማስቀረት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ መንቀሳቀስና የመከላከል ስራዎችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ይህንንም ለማከናወን የጤና ኤክስቴንሽን ስራዎችን በተለይም የወባ ወረርሽኝን ጨምሮ ውሃ ወለድ በሽታዎችንና ሌሎችም ተዛማጅ ችግሮችን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን ዲጂታላይዝድ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በወባ በሽታ የሚሞተው የሰው ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ቁጥር ለመቀነስ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በተለይም በኮሌራ፣ በእብድ ውሻ በሽታ፣ በማጅራት ገትር እና ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ለሚመጣ በሽታ የሚፈጠረውን የስርጭትና የሞት መጠን ለይቶ እና አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባም መግለጻቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
በስድስት ወራት ውስጥ 13 ነጥብ 9 ሚሊየን ለሚሆኑ የወባ ተጠርጣሪ ህሙማን ምርመራ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጃ ዱጉማ ናቸው፡፡