አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ የሊባኖስ መንግስት መዋቅር አካል መሆን እንደሌለበት አሜሪካ አስታወቀች፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ ም/ልዩ መልዕክተኛ ሞርጋን ኦርቴጋስ በሰጡት መግለጫ÷ሂዝቦላህ አዲስ በሚዋቅረው የሊባኖስ መንግስት ውክልና ሊኖረው እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡
ሂዝቦላህ ውክልና የሚኖረው ከሆነ የአሜሪካን ቀይ መስመር እንደማለፍ ይቆጠራል ያሉት ም/ልዩ መልዕክተኛዋ÷ቡድኑ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆኖ ሊባኖሳዊያንን እንዲያሸብር ዋሺንግተን አትፈቅድም ብለዋል፡፡
ሂዝቦላህ አመራሮቹ የተገደሉበት፣ የፈራረሰ እና የተሸነፈ ቡድን መሆኑን ጠቅሰው ፥ ለቡድኑ መዳከም የአሜሪካ ስትራቴጂካዊ አጋር እስራኤል ትልቁን ድርሻ እንደምትወስድ አስገንዝበዋል፡፡
ቡድኑ አንድ ዓመት ከቆየው ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ከእስራኤል ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሱን የገለፁት ሞርጋን ኦርቴጋስ ÷ሂዝቦላህ በአሸባሪነት የሚቀጥልበት ዘመን እንደሚያበቃ አመላክተዋል፡፡
በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ሹመት ያገኙት እና ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ጉብኝት ያደረጉት ም/ልዩ መልዕክተኛዋ÷ሂዝቦላህን በተመለከተ ከሊባኖሱ ፕሬዚዳንት ጋር እንደመከሩ መናገራቸውን አል አራቢያ ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ