አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል ከአንዲት እናት 24 ኪሎ ግራም የሚመዝን ዕጢ በቀዶ ሕክምና መወገዱ ተገልጿል፡፡
የ38 ዓመት ታካሚዋ ወ/ሮ ትሁን ገነቱ በፓዌ ልዩ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ÷ሁለት ሰዓት አካባቢ የወሰደ የተሳካ ከባድ ቀዶ ሕክምና አድርገው ለ2 ዓመታት አብሯቸው የቆየው አላስፈላጊ ዕጢ ተወግዶላቸዋል ተብሏል፡፡
ቀዶ ጥገናው በእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ቡድኑ በማህፀንና የወሊድ ስፔሻሊስት ዶ/ር ማርቆስ አዲሱ የተመራ እንደነበርም የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ሀይሉ ተናግረዋል።
ታካሚዋ በአሁኑ ሰዓት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ መገለጹንም የአዊ ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡