የሀገር ውስጥ ዜና

ሩሲያና ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ

By amele Demisew

February 09, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በጤናው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ተስማሙ።

የሩሲያ ጤና ሚኒስትር ሚካየል ሙራሽኮ እና በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ ውይይት አካሄደዋል።

በውይይታቸው ሁለቱ ሀገራት የህክምና ትምህርትን እና የሙያ ማሻሻያ ስልጠናን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ተስማምተዋል።

ሩሲያ በአዲስ አበባ የነበረውን የቀድሞው የሩሲያ ቀይ መስቀል ያሁኑ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታልን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ድጋፍ ለማደረግ መወሰኗ ተገልጿል።

የጤና ሚኒስትሩ በእናቶች እና ህጻናት ህክምና ዘርፍ ከ80 በላይ ኢትዮጵያዊያን ስፔሻሊስቶች በሩሲያ ስልጠና መውሰዳቸውን ጠቅሰው በሌሎች ዘርፎችም ድጋፍና ስልጠና ለማድረግ ዝግጁ ነን ማለታቸውን ስፑትኒክ ዘግቧል።

በአዲስ አበባ በደጃዝማች ባልቻ ስም የተሰየመው የሩሲያ ቀይ መስቀል ሆስፒታል በአፍሪካ የመጀመሪያው የሩሲያ ሁለገብ የህክምና ተቋም ሲሆን በሩሲያ እና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።