የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጠረ

By Feven Bishaw

February 09, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል  ባለፉት ስድስት ወራት  ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

 

ጨፌ ኦሮሚያ 4ኛ ዓመት 6ኛ የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል።

 

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በጨፌው መደበኛ ጉባኤ ላይ የአስፈጻሚ አካል የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

 

በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ከ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ዜጎች በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

 

የክልሉ ህብረተሰብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በቅርበት ምላሽ ለመስጠትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተደራጀው የቀበሌ አደረጃጀት ውጤት እያስገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

በዚህም ከ49 ሺህ በላይ አመራሮች ተመድበው ህዝቡን በቅርበት በማገልገል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

በኢንቨስትመንት ዘርፍ 10 ሺህ 61 ፕሮጀክቶችን በመቀበል 4 ሺህ 366 የሚሆኑት ለኢንቨስትመንት ቦርድ ቀርበው ውሳኔ እንዲያገኙ መደረጉን አስታውቀዋል።

 

በሪፖርታቸውም የክልሉ መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

 

በዚህም ለታጠቁ አካላት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በማቅረብ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።

 

መንግሥት ባቀረበው ጥሪ የሰላም አማራጭን መርጠው ወደ ሰላም ከመጡ ታጣቂዎች ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረም መቻሉንም አስታውሰዋል።

 

የክልሉ መንግሥት አሁንም ሰላማዊ አማራጭን ለሚመርጡ፣ ልዩነትን በሰላማዊ አማራጭ ብቻ ለመፍታት ፍላጎት ካላቸው አካላት ጋር ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

የሰላም አማራጭን በማይቀበሉና ፍላጎት በሌላቸው አካላት ላይ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቁት።

 

የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የልማት ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።