የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ  በዲፕሎማሲው መስክ ስኬታማ ተግባራትን አከናውናለች – አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

By Feven Bishaw

February 09, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ በዲፕሎማሲው መስክ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የሚያስችሉ አመርቂ ተግባራትን ማከናወኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ፡፡

 

ብልፅግና ፓርቲ ባካሄደው ሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ በተለያዩ መስኮች የተገኙ ውጤቶችን የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች አስተላልፏል።

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ፓርቲው ባሳለፋቸው ውሳኔዎች ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ የብልጽግና የውጭ ግንኙነት ዋና መርህ ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅና ከአካባቢው ሀገሮች ጋር በጋራ መልማትና ማደግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

ብልጽግና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጋራ ልማትና ዕድገትን ለማረጋገጥ አበክሮ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ምስጋኑ፣ ይህን ለማሳካት ትኩረት መስጠቱንና የጎረቤት ሀገራትን ሰላም ለመረጋገጥ ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

 

ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት በግልጽ አቋሟን ማራመድ የጀመረችው በብልጽግና ዘመን መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህ ረገድ የተሄደበት መንገድ ብሔራዊ ጥቅማችንን በአግባቡ ለማስከበር የቻልንበት ነው ብለዋል፡፡

 

ኢትዮጵያ በአካባቢው ያላትን ተፅእኖ ፈጣሪነት በመጠቀም ለቀጣናው ሁለንተናዊ ዕድገትም በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ አብራርተዋል።

 

እንደ አገር የፖለቲካ የኢኮኖሚና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች አዎንታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡