Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ 22 ሺህ ህጻናት ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ትኩረት እንዲደረግ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን በሀገር ውስጥ ባሉ የተለያዩ አማራጮች ለመደገፍ ብሔራዊ የህጻናት የድጋፍና ክብካቤ መመሪያ በአዲስ መልክ ተሻሽሎ በስራ ላይ መዋሉ ተጠቁሟል፡፡

ሚኒስቴሩ መመሪያውን ለማስፈፀምና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህጻናትን ሕይወት ለመታደግ ሰፋፊ የግንዛቤና የማህበረሰብ ንቅናቄ እያካሄደ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሃብት የማሰባሰብና የመደገፍ ሥራ ሲሰራ መቆየቱ ነው የተገለጸው፡፡

ባለፉት ስድሥት ወራት በማህበረሰብ አቀፍ የህፃናት ድጋፍና ክብካቤ 8 ሺህ 356፣ በተቋማት የ1 በመቶ ስፖንሰርሺፕ ድጋፍ 11 ሺህ 160፣ በፎስተር ኬር 1 ሺህ 938 እንዲሁም በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ 1 ሺህ 432 በድምሩ 22 ሺህ 886 ህፃናትን ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉ ተመላክቷል።

እስካሁን እንደሀገር በተሰራው ጠንካራ ቅንጅታዊ ስራ በተለያዩ አማራጭ ፕሮግራሞች የተደገፉ ህፃናት ምጣኔን ከነበረበት 77 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 78 ነጥብ 8 በመቶ ማድረስ መቻሉ ተመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ በተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት መኖራቸው የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም የህፃናቱን መብትና ሁለንተናዊ ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ ባለድርሻና አጋር አካላት ትኩረት እንዲሰጡና በቅንጅት እንዲሰሩ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል።

Exit mobile version