አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋምቤላ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በፓርቲው 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ መክረዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባል ዓለሚቱ ኡሞድ በዚህ ወቅት ÷የፓርቲውን ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በክልሉ አስከታችኛው መዋቅር ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ብለዋል።
ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ያስገኛቸውን ሁለንተናዊ ስኬቶች ይበልጥ በማጠናከር የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
የዛሬው ውይይት ዓላማም በጉባዔው በተላለፉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ በማያዝ ወደ ትግበራ ለመግባት መሆኑን ገልፀዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሺኔ አስቲን በበኩላቸው÷ ፓርቲው ገዢ ትርክቶችን በመገንባት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ሲያከናውናቸው የነበሩ ሥራዎችን በቀጣይ ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል።
እንዲሁም የህዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን የማረጋገጥ ሒደት በትኩረት የሚሰራባቸው ተግባራት ናቸው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።