አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲንን ጦርነት ማስቆም በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ላይ በስልክ መምከራቸውን ተሰምቷል፡፡
ኒዮርክ ፖስትን ጠቅሶ ኣናዶሉ ኤጀንሲ እንደዘገበው፥ ሁለቱ መሪዎች በምን ጉዳይ ላይ እንደተስማሙ በውል ባይታወቅም ለዓመታት የቆየውን የዩክሬን እና ሩሲያን ጦርነት ያለመ የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡
ከውይይቱ በኋላ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ÷ በውይይቱ ፑቲን ጦርነቱ እንዲቆም እንዲሁም ወጣት የሩሲያ እና ዩክሬን ወጣቶችን ሞት ማስቀረት እንደሚፈልግ ገልፀውለኛል ብለዋል፡፡
በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ውስጥ የምስራቅ አውሮፓ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የተሳሳተ እይታ ነበረው ያሉት ትራምፕ ÷ በእርሳቸው አስተዳደር ግን ሦስት ዓመት ሊደፍን የተጠጋው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እንደሚቆም አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ጦርነት የዓለም ጂኦ-ፖለቲካዊ መስተጋብር ተፅዕኖ ውስጥ መውደቁን እና አሁንም የዩከሬን እና ሩሲያ ወጣደሮች በየቀኑ እየሞቱ እንደሚገኙ ጠቅሰው ፥ አሜሪካ ጦርነቱን በፍጥነት ለማስቆም እየሰራች መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄ ዲ ቫንስ በቀጣይ ሣምንት የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪን ለማናገር ቀጥሮ መያዛቸው ተሰምቷል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በቅደመ ምርጫ ወቅት ባደረጉት ቅስቀሳ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን የወታደራዊ ድጋፍ እርዳታ እንደምታቆም እና በምላሹም ሁለቱ ሀገራት ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲመጡ ለማድረግ እሰራለሁ ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
በሚኪያስ አየለ