የሀገር ውስጥ ዜና

የመረዋ-ሶሞዶ-ሰቃና ሊሙ መገንጠያ መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ እየተፋጠነ ነው

By amele Demisew

February 11, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግንባታ መጓተት ገጥሞት የነበረው የመረዋ – ሶሞዶ – ሰቃና ሊሙ መገንጠያ መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል፡፡

በአስተዳደሩ የጅማ አካባቢ የግንባታ ፕሮጀክቶች ጽ/ቤ ም/ሃላፊ ዮናታን ጫኔ (ኢ/ር) ÷ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን እየተከናወነ የሚገኘው ፕሮጀክቱ በ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በጀት ከ4 ዓመት በፊት መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ የመንገድ ፕሮጀክቱ በወሰን ማስክበር፣ በሥራ ተቋራጩ በኩል በነበሩ ውስንነቶች እና መሰል ችግሮች መጓተቱን ነው ያስረዱት፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የመንገድ ፕሮጀክቱን ግንባታ አፈጻጸም ወደ 70 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

በፕሮጀክቱ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የነበሩ የአፈጻጸም መዘግየቶችን ለማካካስ በሙሉ አቅም እየተሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የማና እና የሊሙ ኮሳ ወረዳዎችን አካሎ መዳረሻውን ጀማ ከተማ የሚያደርገውና 94 ኪሎ ሜትሮች የሚሸፍነው የመንገድ ግንባታ ሲጠናቀቅ ቀድሞ ይወስድ የነበረውን 6 ሰዓት የጉዞ ጊዜ ወደ 2 ሰዓት እንደሚያሳጥር ተመላክቷል፡፡

በወርቃፈራው ያለው