አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶማሌ ክልል ጋድ እና በአፋር ክልል ወራንሶ ሁለት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመንግስት እና በግል አጋርነት ለማልማት ጨረታ መውጣቱ ተገልጿል፡፡
ሁለቱ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች 225 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት የኃይል ስብጥሩን ለማስፋት እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የኃይል አማራጮች አቅም ተጠቅማ የኃይል ፍላጎቷን ለማሟላት የግል አልሚዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ የሚያስችል የመንግስትና የግል አጋርነት የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱም ተገልጿል፡፡
ከአሁን ቀደም በመንግሥት እና በግል አጋርነት ማዕቀፍ ከንፋስ ኃይል 300 ሜጋ ዋት ለማመንጨት አሜአ ፓወር ከተሰኘ የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች ኩባንያ ጋር ስምምነት በመፍጠር ወደ ሥራ መገባቱን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡