አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ዛሬ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ መዲናዋ አዲስ አበባ ይጀመራል።
ስብሰባው “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው።
ለስብሰባው የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ምክር ቤቱ ባለፈው ወር 49ኛው የአፍሪካ ሕብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ ምክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የምክር ቤቱ ስብሰባ የአፍሪካ ሕብረት ተቋማትና አደረጃጀቶች፣በምክር ቤቱ ስር የሚገኙ ኮሚቴዎችና ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዲሁም የአጀንዳ 2063 የአፈጻጸም ሪፖርት ያዳምጣልም ተብሏል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ የማካካሻ ፍትህ፣ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ለማግኘት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች፣ አህጉራዊ ሰላምና ደህንነት፣ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አፈጻጸምና አህጉራዊ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር፣ግብርናና የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ ስርዓተ ጾታና ወጣቶችን ማብቃት እንዲሁም የተቋማትና አደረጃጀቶች ምርጫ ውይይት ከሚደረገባቸው ዋንኛ አጀንዳዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በህብረቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ምክር ቤቱ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ስር የሚገኙ የስድስት ኮሚሽነሮች ምርጫ የሚደረግ ሲሆን ፥ ምርጫው የስራ ጊዜያቸውን ባጠናቀቁ ኮሚሽነሮች ምትክ የሚደረግ ነውም ተብሏል።
በተጨማሪም የአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት የአምስት አባላት ምርጫ ይደረጋል ተብሏል።
ኢትዮጵያ ለሶስት ዓመታት (በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2025 እስከ 2027) ድረስ ለሚቆየው የምክር ቤት የአባልነት ዘመን እንደምትወዳደርም ይጠበቃል።
የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም ለሚከናወነው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚቀርቡ አጀንዳዎችንም ያፀድቃልም ተብሏል።
የአፍሪካ ሕብረት ተቋማትና አደረጃጀቶች መግለጫዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶች ዛሬ እንደሚካሄዱ የሕብረቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የፊታችን ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።