ስፓርት

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ሻምፒዮን ሆነ

By yeshambel Mihert

February 12, 2025

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ8ኛው ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር ዛሬ በፍፃሜ በተደረገ የወንዶች እግር ኳስ ጨዋታ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሶማሌ ክልልን 3 ለ 1 በማሸነፍ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ሻምፒዮን ሆኗል።

በወላይታ ሶዶ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 8ኛው ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ምዘና ውድድር ዛሬ ተጠናቋል።

ከጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው ውድድር አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ቅርጫት ኳስ፣ ቦክስ፣ ፖራኦሎምፒክ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ እጅ ኳስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ እና ውሃ ዋና ስፖርቶች ምዘና ተደርጎባቸው ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል።

አስቀድሞ ለደረጃ በተደረገ ጨዋታ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲዳማ ክልልን በመለያ ምት አሸንፎ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ኦሮሚያ ክልል የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን÷ አዲስ አበባ ከተማ 2ኛ እና አማራ ክልል 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

ውድድሩ ሀገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚጠቅም የተገለጸ ሲሆን÷በውድድሩ ላይ ጥሩ ውጤት ያመጡ ከ100 በላይ ታዳጊ ስፖርተኞች ወደ ማሰልጠኛ እንዲገቡ ተመልምለዋል።

በእንዳልካቸው ወዳጄ