Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኦሮሚያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የወባ በሽታ ስርጭት ቀነሰ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የወባ በሽታ ስርጭት መቀነሱ ተገለፀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ክበበው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደተናገሩት÷ በክልሉ በተካሄደው የወባ ማጥፋት ንቅናቄ ስርጭቱን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል፡፡

በክልሉ በየሳምንቱ ከ160 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ይያዙ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት በየሳምንቱ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአማካይ ከ60 ሺህ እንደማይበልጥ ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክተር ዶክተር እንዳለ ሳህሌ በበኩላቸው÷ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል በተሰራው ሥራ ውጤት መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም የበሽታውን ስርጭት በመቀነስ የክልሉን የወባ በሽታ ጫና 78 በመቶ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የመከላከል ሥራዎች አሁንም ተጠናክረው መቀጠላቸውን እና የበሽታውን ስርጭት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን ክልሎቹ ገልጸዋል።

በዙፋን ካሳሁን

Exit mobile version