Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ የተቀመጡ ውሳኔዎች እንዲሳኩ የፌዴራል ተቋማት የብልጽግና አደረጃጀት አባላት ሚና የላቀ ነው – አለሙ ስሜ (ዶ/ር)

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎች ግባቸውን እንዲመቱ የፌዴራል ተቋማት ብልጽግና አደረጃጀት አባላት ሚና የላቀ ሊሆን እንደሚገባው ተገለጸ።

በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ የፌዴራል ተቋማት ብልጽግና አደረጃጀት አባላት ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

ውይይቱ በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ ወጥ የሆነ ግንዛቤ በመያዝ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲከወኑ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የፌዴራል ተቋማት ብልጽግና አደረጃጀት ሰብሳቢ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዳሉት ÷ጉባዔው በሁሉም መስክ ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል።

በፓርቲው የመጀመሪያው ጉባዔ ላይ የተቀመጡ አቅጫዎች ስኬታማ ሆነው መፈጸማቸውን በሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ መገምገሙን አንስተዋል፡፡

ለዚህም የፌዴራል ተቋማት ብልጽግና አደረጃጀት ሚና አወንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው÷በሁለተኛው መደበኛ ጉባዔ የተቀመጡ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችም ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበሩ የአባላቱ ሚና ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

ውሳኔዎችና አቅጣጫዎቹ በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውስጥ ተካተው መተግበር እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ለዚህም ተቋማት ከያዙት ዕቅዶች ጋር በተናበበ መልኩ ለመተግበር መስራት እንደሚገባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በውሳኔና አቅጣጫዎች ላይ የመንግሥት ሰራተኞችና ህዝቡ ግንዛቤ እንዲጨብጥ በማድረግ ለሀገራዊ ግቦች ስኬት በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የፌዴራል ተቋማት ብልጽግና አደረጃጀት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በውሳኔ እና አቅጣጫዎች ላይ አመራሩ ወጥ የሆነ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የፓርቲው አመራር እና አባላትን ብቃትና ጥራት በማሳደግ ጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ስራውን ማጠናከር፣ ብሄራዊነት ገዥ ትርክት እንዲሆን መስራት፣ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታን ጨምሮ ስምንት አቅጫዎች መቀመጣቸውን ጠቅሰዋል።

የጉባዔው ውሳኔዎች እስከታች መውረድ እንዳለባቸው ገልጸው÷ለዚህም ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

Exit mobile version