Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ምርታማነት ተሞክሮዋን አካፈለች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በ”ዓለም አቀፍ የመስኖና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነት ጉባዔ” ላይ በዘላቂ ልማት ላይ ያስመዘገበችውን ውጤት በተሞክሮነት አካፍላለች፡፡

በአዲስ አባባ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው በ”ዓለም አቀፍ የመስኖና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነት ጉባዔ” ሁለተኛ ቀኑን ይዟል፡፡

በጉባዔው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ ሚኒስትሮች እና የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)÷ኢትዮጵያ በዘላቂ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ረገድ እያስመዘገበች ያለውን ውጤት ለተሳታፊ ሀገራት ተወካዮች አብራርተዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና አካባቢን በመጠበቅ ተጨባጭ የሚባል ለውጥ እያደረገች መሆኗን ጠቅሰው ፥ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል የያዘቸው እቅድ አካል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሯ አክለውም እስካሁን ኢትዮጵያ 40 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል የሀገሪቱን የደን ሽፋን 6 በመቶ ማሳደግ መቻሏን አስገንዝበዋል፡፡

ከተተከሉት ችግኞች መካከል ፍራፍሬዎች ከፍተኛ መጠን ያላቸው እንደሆኑ መጠቆማቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን በመቻል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመቀነስ እና ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት ኢትዮጵያ በምግብ አቅርቦትና ተደራሽነት የምግብ ዋስትናን እንድታረጋግጥ የሚያደርግ ንቅናቄ መሆኑን ጠቅሰው÷ይህም ጠንካራ እና የበለፀገ የምግብ ሥርዓትን መዘርጋት እንደሚያስችል ነው የተናገሩት፡፡

ንቅናቄዎቹ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ምርጥ ተሞክሮ መሆናቸውን አውስተው ፥ ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታከናውነቸው ተግባራት የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋምና በምግብ ዋስትና ላይ ያላትን አቋም እንደሚያሳዩም አመልክተዋል፡፡

Exit mobile version