አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 9ኛ መደበኛ ጉባኤ በተለያዩ አዋጆች ላይ ተወያይቶ አፀደቀ።
በጉባኤው ከፀደቁት አዋጆች መካከል የክልሉ መንግስት የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ይገኝበታል።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም÷ የዚህ አዋጅ መጽደቅ ማንኛውም የመንግስት አመራር አባል ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ የሚያደርግ በመሆኑ ለህዝብ ተጠቃሚነትና የህግ የበላይነት መረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ይህም በአስተዳደር ተቋማት የሚሰጡ ውሳኔዎችና የሚወጡ መመሪያዎች በሰዎች መብቶችና ጥቅሞችን በህግ መምራት በማስፈለጉ እንደሆነ አሰረድተዋል።
ለዚህም በአስተዳደር ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ግለሰብ የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎቹን ህጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ስርዓት በመደንገግ አስተዳደራዊ ፍትህን ማረጋገጥ ለማስቻል እንደሆነም አመላክተዋል።
ሌላው ለምክር ቤቱ ቀርቦ የፀደቀው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ማሻሻያ አዋጅ ሲሆን፤ አዋጁ የመንግስት አሰራር በግልፅነትና ተጠያቂነት ማከናወን ይበልጥ እንዲጠናከር ለማስቻል እንደሆነም አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።
የጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ማሻሻያ አዋጅ ሌላው በዕለቱ የጸደቀ አዋጅ ሲሆን፤ ይህም የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅና ፍትህን ለማስፈን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ የጥብቅና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቀጣይነትና ዋስትና ያለው የጥብቅና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል አዋጁን ማሻሻል ማስፈለጉን አብራርተዋል።
የምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ደሴ ጥላሁን በበኩላቸው፤ አዋጆቹ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ግብአት በማሰባሰብ እንዲዳብሩ ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ምክር ቤቱም በአዋጆቹ ላይ በስፋት ከመከረ በኋላ አፅድቋል።