አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጃፓን ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እያደረገች ያለውን ከፍተኛ አበርክቶ እንደምታደንቅ ገለጸች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከጃፓን የውጭ ጉዳይ ፓርላሜንታሪ ምክትል ሚኒስትር ኤሪ አርፊያ ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድል በመፍጠሩ የጃፓን ኩባንያዎች በኢንቨስትመንት እንዲሠማሩ ጠይቀዋል።
አምባሳደሩ የቀይ ባሕር እና የአፍሪካ ቀንድ የደኀንነት ስጋት ቀጣናዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ የጋራ ስጋት መሆኑን አንስተው፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እያደረገች ያለውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ በኢኮኖሚ ግንኙነት አጠናክራ እንድትቀጥል እና መንግሥታዊ የልማት ድጋፏንም እንድታጠናክር አረጋግጠዋል።
ኤሪ አርፊያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ቁልፍ መሆኗን ገልጸው፤ ጃፓን ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እያደረገችው ያለውን ከፍተኛ አበርክቶ ታደንቃለች ነው ያሉት።
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የበለጠ አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።