Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጦር መሳሪያ በማስፈራራት ስርቆት የፈጸመው ግለሰብ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እረኞችን በጦር መሳሪያ በማስፈራራት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቤት እንስሳት የሰረቀው ግለሰብ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጥቷል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ደምሰው ታደሰ መሌ በተባለ ተከሳሽ ላይ ማስረጃ መርምሮና አመዛዝኖ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል።

የዞኑ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) አንቀጽ 35 እና አንቀጽ 671 ንዑስ ቁጥር (2) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፉን ጠቅሶ ተደራራቢ ከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ አቅርቦበት ነበር፡፡

ተከሳሹ በጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ በዞኑ ዳራ ወረዳ ማንቃታ ዋሪዮ ቀበሌ ጎጢ ጉዳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ለራሱ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ከሌሎች ለጊዜው ካልተያዙ ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን በአካባቢው ከብት ሲጠብቁ የነበሩ እረኞችን በጦር መሳሪያ አስፈራርቶ እንዲሸሹ በማድረግ የአምስት የግል ተበዳይ አርሶ አደሮች ንብረት የሆኑትን 1 ሚሊየን 591 ሺህ ብር የሚገመቱ 34 ከብቶች፣ 49 በጎች እና ሶስት አህዮችን በግዳጅ የወሰደና የሰወረ መሆኑ በክሱ ዝርዝር ተጠቅሷል።

ተከሳሹ በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውሎና ፍርድ ቤት ቀርቦ የክስ ዝርዝር ከደረሰው በኋላ የወንጀል ተግባሩን ክዶ መከራከሩን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰው ማስረጃ አቅርቦ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ማስረጃውን መርምሮ ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከል ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሹ ማስተባበል አለመቻሉ ጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበታል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮና ይዞ ተከሳሹንም ሆነ ሌላውን ያስተምራል በማለት በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version