አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከቻይና መንግሥት የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ ተወካይ ሊ ዩሺ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ቀንድ እና አሕጉራዊ ሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ ለልዩ ተወካዩ ባደረጉት ገለጻ፤ ሀገራቱ በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መመስረታቸውን አስታውሰዋል።
ቻይና ለኢትዮጵያ የልማት ጥረቶች ቁልፍ አጋር መሆኗንም አረጋግጠዋል።
ልዩ ተወካዩ ሊ ዩሺ በበኩላቸው÷ በየጊዜው የሚደረጉ የከፍተኛ ባለሥልጣናት የጉብኝት ልውውጦች የሀገራቱ ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ማሳያ ነውም ብለዋል።
በቻይና አፍሪካ መድረክ (ፎካክ) የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን ንግድ እና ኢንቨስትመንት በማስፋፋት እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ የቻይና ድጋፍ እንደሚጠናከር መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።