የሀገር ውስጥ ዜና

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

By amele Demisew

February 15, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት ፋይሌመን ያንግን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በሰጡት ማብራሪያ÷ ከተባበሩት መንግሥታት አመራሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድርጋቸውን ጠቅሰዋል።

ከተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያና የመንግሥታቱ ድርጅት የረጅም ዘመን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንና መግባባት ላይ መድረሳቸውን አንስተዋል።

በተመሳሳይ ዛሬ ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት ፋይሌመን ያንግ ጋር የጠቅላላ ጉባኤው ስልጣንና ተግባር እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ በነበረው የተቋሙ ሪፎርም ላይ ያተኮረ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በተለይም አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ተገቢውን ውክልና በምታገኝበት ጉዳይ ላይ ጠቃሚ ሀሳቦች መለዋወጣቸውን እንደገለጹ የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የቀድሞ የካሜሮን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የጠቅላላ ጉባኤው ፕሬዝዳንት ፋይሌመን ያንግ በበኩላቸው÷ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በነበራቸው ውይይት የተባበሩት መንግሥታትን እና አፍሪካን በተመለከተ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቁልፍ የሆነች ሀገር ናት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ በተባበሩት መንግስታት ቻርተር በጽኑ የምትታመን ወሳኝ አባል ሀገር መሆኗንም ገልጸዋል።