የሀገር ውስጥ ዜና

ሚኒስቴሩ ያስገነባውን የግብርና ሜካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል አስመረቀ

By amele Demisew

February 15, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ እና የደቡብ ኮሪያ መንግስት ትብብር የተገነባውን የግብርና ሜካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል ዛሬ አስመረቀ።

ማዕከሉ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች የጥራት ፍተሻ፣ የጥገናና የተለያዩ ባለሙያዎችን ማሰልጠን የሚያስችል ነው።

ዛሬ ተመርቆ ወደ ስራ የገባው ተቋም በግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት፣ የተጀመሩ ስራዎችን ለማስቀጠል እና የሜካናይዜሽን ተደራሽነትን ለማስፋት እንደሚረዳ ተጠቁሟል።

በምረቃ ስነስርአቱ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የግብርናው ዘርፍ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል ያሉ ሲሆን የማዕከሉ ምረቃ ለጀመርነው ጉዞ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

ማዕከሉ የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽኖችን ጥራት የምናረጋግጥበት፣ ምርምሮች የምናደርግበት እና የሰው ኃይልን የምናሰለጥንበት ነው ሲሉ አክለዋል።

በምረቃ ስነስርአቱ በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር እና የሁለቱ ሀገራት የግብርና እና ሜካናይዜሽን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በቅድስት አባተ