የሀገር ውስጥ ዜና

መዲናዋ እያስመዘገበች ያለው እድገት የሚደነቅ መሆኑን የሀገራት መሪዎች ተናገሩ

By Meseret Awoke

February 16, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ እያስመዘገበች ያለው ፈጣን እድገት የሚደነቅ መሆኑን ከአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄዱ ሁነቶች የተሳተፉ የሀገራት መሪዎችና ተሳታፊዎች መናገራቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ የጉባኤውን ውሎ እና ሌሎች የተካሄዱ ሁነቶችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው ዛሬ የአፍሪካ የደህንነትና ፀጥታ ምክር ቤትን ጨምሮ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት መካሔዳቸውን ገልፀው፥ በውይይቱ ላይ ሀገራት የሰላምና ፀጥታ ስራዎቻቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው መነሳቱንም ተናግረዋል።

በተለይም ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለው እሳቤ ከቃል ባለፈ በተግባር ለማመላከት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አፅንኦት ተሰጥቷል ብለዋል።

በሌላ በኩልም የአፍሪካ በሽታ መከላከል ማእከል በአጭር ጊዜ ውስጥ እያከናወነ ያለውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማጠናከር እንዳለበትም እንዲሁ።

በተመሳሳይ የአፍሪካ ሕብረት እያካሔደ ያለውን ሪፎርም ሁሉንም ሀገራት ያማከለ መሆን እንዳለበት መገለጹንም አብራርተዋል።

ይህም የህብረቱን ቁመና በተሻለ መልኩ ለማደራጀት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ነው መገለጹን አንስተዋል።

በሌላ በኩል ዛሬ በነበሩ የተናጥልና የጋራ ውይይቶች በተለይም አዲስ አበባ እያስመዘገበች ያለው ፈጣን እድገት የሚደነቅ መሆኑን የሀገራት መሪዎችና ሌሎች የጉባኤው ተሳታፊዎች መናገራቸውን ነው የገለጹት።

በዚህም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ተሞክሮ የሚወስዱባቸው ተግባራት እንዳሉ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ይህም በአንድ አመት ውስጥ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት ተከናውነው ማየታቸውን መስከረዋል ነው ያሉት።