አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር አሁና ኤዚያኮንዋ ጋር ተወያይተዋል።
በዚሁ ወቅት ዳይሬክተሯ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ በተጀመረው የመልሶ ማልማት ሥራ መደነቃቸውን ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
በከተማው ልማት የነዋሪዎች ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ አካታች የልማት ስትራቴጂ መተግበሩን የልማት ተነሺዎችን መኖሪያ ቤት በጎበኙበት ወቅት ከተነሺዎቹ አንደበት መስማታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸውልኛል ብለዋል ከንቲባዋ፡፡
እንዲሁም ይህ ለመላው አፍሪካ ከተሞች እንደ ልምድ ሊስፋፋ እና አዲስ አበባም ይህን ሚናዋን ልትወጣ እንደሚገባም ዳይሬክተሯ በውይይቱ ላይ ማመላከታቸው ተገልጿል፡፡
በቀጣይም በከተማዋ በሚሠሩ የልማት እና ሰው ተኮር ሥራዎች ላይ በትብብር ለመሥራት ከመግባባት ላይ ተደርሷል ተብሏል፡፡