የሀገር ውስጥ ዜና

ቋሚ የስራ እድል የተፈጠረላቸው 13 ሺህ 527 ወጣቶች ተመረቁ

By yeshambel Mihert

February 18, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ” መርሐ ግብርን ያጠናቀቁና ቋሚ የስራ እድል የተፈጠረላቸው 13 ሺህ 527 ወጣቶችን አስመረቁ፡፡

ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ “ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ” መርሐ ግብር በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች ወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የከተማዋ ወጣቶች በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከተጀመሩ ስትራቴጂዎች አንደኛው መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የከተማዋን ወጣቶች ክህሎት በስራ ላይ ልምምድ ብቻ የሚያበቃ ባለመሆኑ ወደ ስራ ሲገቡ ይበልጥ ራሳቸውን በብቃት እንዲያሳድጉ፣ ስራን ከማማረጥ በመውጣት እና ጠንካራ የስራ ባህልን በማዳበር በተፈጠርላቸው የስራ እድል በሙሉ እንዲጠቀሙም አሳስበዋል፡፡

በቀጣይ 15 ሺህ የከተማዋን ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ 3ኛ ዙር ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ መርሐ ግብር ዛሬ በይፋ መጀመሩን በመግለጽ ወጣቶች በዚህ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በወጣቶቹ የስራ ላይ ልምምድ ወቅት የገንዘብ ድጋፍ ያደረገውን የዓለም ባንክ ጨምሮ ለመርሐ ግብሩ መሳካት አስተዋፅዖ ያደረጉ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የከተማዋ የስራና ክህሎት ቢሮ፣ ባለሃብቶች እንዲሁም መርሐግብሩን ላሳኩ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡