አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት በዛሬው የሶስተኛ ቀን የጉባኤ ውሎው የምክር ቤቱ መቀመጫ ቁጥር እና የክልሉ አርማ ማሻሻያዎች የተካተቱበትን የክልሉን ህገ-መንግስት ማሻሻያ አዋጅን በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡
የክልሉን ህገ መንግስት ማሻሻል ያስፈለገው እያደገ የመጣውን የውክልና ጥያቄ በመመለስ ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለማጠናከር መሆኑ ተብራርቷል።
በክልሉ የሚገኙ የሁሉም የወረዳ ምክር ቤቶች የህገ መንግስት ማሻሻያ ሃሳቡ ላይ በመወያየት ከሁለት ሶስተኛ በላይ በሆነ ድምፅ ማሻሻያውን ቀደም ብለው እንዳፀደቁት ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ቀደም ሲል የነበረው የምክር ቤቱ መቀመጫ ከ100 መቀመጫ በላይ እንዳይኖረው የሚደነግግ ሲሆን÷ ዛሬ የጸደቀው የክልሉ ህገ-መንግስት ማሻሻያ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ ከ99 ወደ 160 መቀመጫ ከፍ እንዲል የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡
በክልሉ የተጨመሩ የወረዳ እና ቀበሌ መዋቅሮችን የህዝብ ውክልና ጥያቄ ለመመለስ የምክር ቤቱን መቀመጫ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ምክር ቤቱ መክሮበታል።
ክልሉ ህብረ ብሄራዊ በመሆኑ በሚያድገው የምክር ቤቱ መቀመጫ በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ብሄረሰቦችን ውክልና በማሳደግ አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲጎለብት ይረዳልም ተብሏል።
በሌላ በኩል በክልሉ ጥቅም ላይ የነበረው የክልሉ አርማም ክልሉ አሁን የሚገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲሻሻል ምክር ቤቱ መወሰኑን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡