Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የህብረቱ ጉባኤ ስኬታማ ነበር -የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 38ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በርካታ እንግዶችን በተሳካ ሁኔታ ያስተናገደ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በሰጡት መግለጫ ÷ ጉባዔው ኢትዮጵያ ደምቃ የታየችበትና ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል።

በጉባዔው ከታደሙት ከ17 ሺህ በላይ እንግዶች ውስጥ ከ12 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከውጪ የመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከ1 ዓመት በላይ ዝግጅት ያደረገችበት እንደነበር ያነሱት አምባሳደር ብርቱካን ፥ የቀድሞ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ 101 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተለያዩ መስኮች ተሳትፈዋል ብለዋል።

ደረጃውን የጠበቀ የሎጂስቲክስና ትራንስፖርት አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን ÷ 882 ደረጃቸውን የጠበቁ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ ውለዋል ነው ያሉት።

እንግዶች ከ12 ሺህ በላይ ፈጣን የቪዛ አገልግሎት ማግኘታቸውንም አንስተዋል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን በርካታ መድረኮች በተለያዩ ተቋማት የተከወኑ ሲሆን ÷ ነባርና አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማሳየትና ማስተዋወቅም ተችሏል ነው የተባለው።

ኢትዮጵያ በዚህ ጉባኤ የአፍሪካ መዲናነቷ ጎልቶ የወጣበትና የማህበረሰቡ እንግዳ ተቀባይነት የተደነቀበት እንደነበርም ተነስቷል።

እስከ ሥድስት ቀናት የነበረው የእንግዶች ቆይታ እጅግ የተሳካ እንደነበር አምባሳደሯ ተናግረው ፥ ለጉባዔው መሳካት ለተባበሩ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሃይማኖት ወንድይራድ

Exit mobile version