የሀገር ውስጥ ዜና

የከተሞችን ልማት ለማፋጠን በትኩረትና በቅንጅት መስራት ይገባል- ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

By yeshambel Mihert

February 19, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የተመራ ልዑክ በወላይታ ሶዶ ከተማ የድጋፍና ክትትል ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡

ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ከክትትል ሥራው ጋር በተያያዘ ከወላይታ ዞንና ሶዶ ከተማ አመራሮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ሚኒስትሯ÷በኢትዮጵያ በ12 ክልሎች ለሚገኙ 27 ከተሞች የድጋፍና ክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክትትል ሥራው የ10 ዓመት የልማት ግቦችን መነሻ በማድረግ በከተማ ልማት ዘርፍ የሚከናወኑ ሥራዎች ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለመገምገም ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ በጥንካሬ የተመዘገቡት ለማጎልበትና ያጋጠሙ ችግሮችን እና ተግዳሮቶችን በመለየት ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል።

በሚኒስትሯ ለተመራው ልዑክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር ልማት እና የመሠረተ ልማት ሥራዎች አፈጻጸም ሪፖርት መቅረቡን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡