የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያና ሩሲያ የረጅም ጊዜ ወዳጅነት በምጣኔ ሃብታዊ ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል- አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ

By yeshambel Mihert

February 19, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና ሩሲያ የረጅም ጊዜ ወዳጅነት በምጣኔ ሃብታዊ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ ገለጹ፡፡

አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ በሩሲያ ፌዴራል ጉባኤ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊቀመንበር በቫለቲና ማትቬንኮ የተመራ የልዑካን ቡድንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገረዋል፡፡

በዚሁ ወቅት አፈጉባዔ ታገሰ÷ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም ጊዜ ወዳጅነት እንዳላት ገልጸው ወዳጅነቱ በምጣኔ ሃብታዊ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ሩሲያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም ጠቅሰው÷ ግንኙነቱ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በፓርላሜንታዊ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና የንግዱን ማሕበረሰብ ያሳተፉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አፈ-ጉባኤው ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የብሪክስ አባል ሀገራት እንደመሆናቸው፣ በብሪክስ መድረክ ትብብራቸውን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ መገለጹን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

የሩሲያ ፌዴራል ጉባኤ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊቀመንበር ቫለቲና ማትቬንኮ በበኩላቸው÷የሁለቱን ሀገራት የቆየ የወዳጅነት ግንኙነት በምጣኔ ሃብት፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ለማስቀጠል ሀገራቸው ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል፡