አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን መከላከል የሁሉም አጀንዳ እንዲሆን መሥራት ይጠበቃል ሲሉ የሴቶች ኮከስ የበላይ ጠባቂና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ -ጉባዔ ሎሚ በዶ አሳሰቡ።
የሴቶችና ሕጻናት መብቶችን አስመልክቶ የወጡ ሕጎችና ዓለምአቀፍ ስምምነቶች አፈፃፀም በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ በትክክል መፈተሽና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል፡፡
ችግሩ ከመድረክ ውይይት በላይ ነው፤ ማኅበረሰቡ ጉዳዩን አጀንዳው እንዲያደርገው በማስቻል የመፍትሔ አካል መሆን አለበት ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
በውክልና ሥራ ወቅት የሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲሁም ጥቃቶችን መከላከል ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።
የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴዔታ መሠረት ኃይሌ በበኩላቸው፥ የሴቶችና ሕጻናት ጥቃት እየጨመረ በመሆኑ በሀገራዊ ምክርክር ጭምር አጀንዳ ሆኖ ችግሩ ሊፈታ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
እንደነዚህ ያሉ አስከፊ ተግባራትን እየተለማመድን ነው፤ ሁሉም አካል የችግሩን አሳሳቢነት ቆም ብሎ በማየት ለመፍትሔው ሊተጋ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡