የሀገር ውስጥ ዜና

በሽረ እንዳስላሴ በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት ድጋፍ እየተገነባ ያለው ት/ቤት በቀጣዩ ዓመት ይጠናቀቃል

By Feven Bishaw

February 20, 2025

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል ሽረ እንዳስላሴ ከተማ በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ድጋፍ እየተገነባ የሚገኘው 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በቀጣዩ ዓመት ተጠናቅቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

የከተማው የትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ኃላፊ ገብረመድህን ወልደ ጊዮርጊስ እንዳሉት ÷ ትምህርት ቤቱ እየተገነባ የሚገኘው የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት በሰጠው የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ነው።

ግንባታው በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው÷ በቀጣዩ ዓመት ተጠናቅቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ ሲጠናቀቅም በሁለት ፈረቃ 1 ሺህ 600 ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ትምህርት ቤቱ ቤተ-ሙከራዎችና ቤተ መጽሐፍት እንዲሁም ለአስተዳደር እና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡