የሀገር ውስጥ ዜና

ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊተላለፉ የነበሩ የመገናኛ ሬዲዮኖች ተያዙ

By yeshambel Mihert

February 22, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰሜን ሸዋ ለሚንቀሳቀሰው የሸኔ ሽብር ቡድን ሊተላለፉ የነበሩ የመገናኛ ሬዲዮኖች መያዛቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ÷የመገናኛ ሬዲዮኖቹ የደቡብ ቀጣና በሚል ከሚጠራው የሸኔ የሽብር ቡድን ክንፍ የተላኩ መሆኑን በመረጃ ስምሪት ተረጋግጦ ክትትል ሲደረግ እንደነበር አመላክቷል፡፡

የመገናኛ ሬዲዮኖች በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ሱሉልታ ልዩ ስሙ ሚዛን የሚባል አካባቢ በጸጥታ ኃይሎች አማካኝነት መያዛቸው ተገልጿል፡፡

በዚህ ሕገ-ወጥ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን ትስስር በመለየት እርምጃ መወሰዱን የገለጸው አገልግሎቱ÷ቀደም ባሉት ጊዜያትም የሽብር ቡድኑን በሎጀስቲክስ፣ በመሣሪያና በፋይናንስ ለማጠናከር ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች የተቀናጀ የመረጃ ስምሪት በማከናወን ከፌዴራልና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሲከሽፉ እንደነበር ገልጿል፡፡

ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት የደምብ ልብሶችና ሌሎችም ቁሶች ተጠቃሽ መሆናቸውን አስታውሷል፡፡

በሰሜን ኬንያ የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ሽብር ቡድን የሀገሪቱ የጸጥታ አካላት ባከናወኑት የተቀናጀ ኦፕሬሽን ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሶበት እየተበተነ መሆኑን አገልግሎቱ ለፋና ዲጅታል በላከው መረጃ አስታውሷል፡፡