የሀገር ውስጥ ዜና

ስንጾም የፍቅርና የምህረት ሥራዎችን በመስራት ሊሆን ይገባል – ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ

By Feven Bishaw

February 23, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ በነገው ዕለት የሚገባውን ዐቢይ ፆም አስመልክተው አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ለፋና ዲጂታል በላኩት መልዕክት÷ የዐቢይ ጾም ስንጾም የእግዚአብሔር ምህረት እንዲበዛልን በጾምና በጸሎት ይበልጥ ጠንክረን ካለን ላይ ለሌላቸው በማካፈል ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ንስሐ በመግባት ከሰዎችና ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቅ ግንኙነታችንን ማደስና ማጠንከር፣ መጾም እና መጸለይ፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ የፍቅርና የምህረት ሥራዎችን በመስራት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዓቢይ ጾም ወራት እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን አንድነታችንን፣ ቤተሰባዊነታችንን እንዲሁም ኢትዮጵያዊነታችንን አክብረንና ተከባብረን ወደን እና ተዋደን በመኖር እንድናጠነክረው ኃይልን እንዲሰጠን በጾምና በጸሎት ከልብ እንለምነው ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ክፉ ከመናገር፣ ከመስማትና ከማየት መታቀብ የጾማችን አካል ይሁን ሲሉም ምዕመኑን አሳስበዋል፡፡