አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልፅግና ፓርቲ ህብረተሰቡን በማሳተፍና በማስተባበር በርካታ የህዝብ ጥያቄዎችን እየመለሰ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ ተናገሩ።
በቦንጋ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የህዝብ ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ÷ ብልፅግና ፓርቲ ህብረተሰቡን በማሳተፍና በማስተባበር በርካታ ጥያቄዎች መልሷል ብለዋል።
ፓርቲው በመጀመሪያው መደበኛ ጉባዔው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎችና ውሳኔዎችን መሰረት በማደረግ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በአዲስ መልክ እንዲደራጅ መደረጉ አንዱ ማሳያ ነውም ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔው ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ላይም የጋራ አረዳድ በመያዝና በመስማማት ቀጣይ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት በጋራ መትጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
መድረኩ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ውጤታማ ስራዎችን የበለጠ ለማጠናከር መዘጋጀቱን ያነሱት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ሲል ኢዜአ ዘግቧል።