አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቻይና የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሥራዎችን ለማጠናከር የሚያስችል የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡
ውይይቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከቻይና የዓለመ አቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የተመራን ልዑክ ጋር ነው በአዲስ አበባ ያካሄዱት፡፡
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ከልዑኩ ጋር በሀገራቱ የንግድ ግንኙነትና ፕሮሞሽን ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ፖሊሲ ተግባራዊ እያደረገች መሆኗን እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር የሚያስችል ገለፃ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ቻይና በቀጣይ ሐምሌ ወር በምታዘጋጀው 3ኛው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ግብዣ መቅረቡን ጠቅሰው÷ በግብዣው መሰረት የኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ በኤክስፖው እንደሚሳተፍ አመላክተዋል፡፡