ስፓርት

መቻል 21 ሚሊየን ብር እንዲሁም ሲዳማ ቡና 18 ሚሊየን ብር ተቀጡ

By Melaku Gedif

February 24, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ተሳታፊ የሆነው መቻል እግር ኳስ ክለብ የ21 ሚሊየን ብር እንዲሁም ሲዳማ ቡና የ18 ሚሊየን ብር ቅጣት የተላለፈባቸው መሆኑን የሊጉ የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ÷በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የክለቦች የክፍያ ሥርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1/2016 አንቀጽ 7 በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት በ4 ክለቦች እና በ15 ተጫዋቾች ላይ ምርመራ አካሂዷል፡፡

በምርመራውም ክለቦቹ የቅድመ ክፍያ (በሶስተኛ ወገን) በመክፈላቸው እና ተጫዋቾቹ በመቀበላቸው በአንቀጽ 5 የተከለከሉ ተግባራት ስር የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የጣሱ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

በመቻል እግር ኳስ ክለብ በተደረገው ምርመራ የክለቡ 7 ተጫዋቾች የቅደመ ክፍያ ገንዘብ መቀበላቸው የተረጋገጠ ሲሆን÷በዚህም ክለቡ በእያንዳንዱ ተጫዋች የ3 ሚሊየን ብር በአጠቃላይ የ21 ሚሊየን ብር ቅጣት ተላልፎበታል፡፡

ከክለቡ በተጨማሪ ተጫዋቾች የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ እና የከፈሉበትን ደረሰኝ በሰባት ቀናት ውስጥ ለአክሲዮን ማህበሩ እንዲያሳውቁ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ በሲዳማ ቡና እግር ኳስ ቡድን በተደረገው ምርመራ 6 ተጫዋቾች የቅድመ ክፍያ ገንዘብ ከአክሲዮን ማህበሩ መመሪያ ውጭ መቀበላቸው የተረጋገጠ ሲሆን÷ ክለቡ በአጠቃላይ የ18 ሚሊየን ብር ቅጣት ተላልፎበታል፡፡

በተጨማሪ ስድስቱ ተጫዋቾች የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ እና የከፈሉበትን ደረሰኝ በሰባት ቀናት ውስጥ ለአክሲዮን ማህበሩ እንዲያሳውቁ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡

በሌላ በኩል የመቐለ 70 እንደርታ እና ሃዋሳ ከተማ አንድ አንድ ተጫዋቾች የቅድመ ክፍያ ገንዘብ በመቀበላቸው እያንዳንዳቸው የ3 ሚሊየን ብር የገንዘብ ቅጣት የተላለፈባቸው ሲሆን÷በተጫዋቾቹ ላይም የ200 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፏል፡፡

በኮሚቴው ቅጣት የተጣለባቸው ቡድኖች ቅጣታቸውን ጨርሰው የክፍያ ደረሰኛቸውን ለአክሲዮን ማህበሩ እስከሚያሳውቁ ድረስ ከውድድር ታግደው እንደሚቆዩ የአክሲዮን ማህበሩ መረጃ አመላክቷል፡፡