የሀገር ውስጥ ዜና

የሐረሪ ክልል ለከሚሴ ሆስፒታል የ6 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

By yeshambel Mihert

February 25, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሐረሪ ክልል ለአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ከሚሴ አጠቃላይ ሆስፒታል ግምታቸው ከ6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የተለያዩ የህክምና ግብዓቶችና መሣሪያዎችን ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሂ ለኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ አስረክበዋል።

ሚኒስትሯ በርክክቡ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ እርስ በርስ መደጋገፍ በጤናው ዘርፍ የተያዘውን ግብ ለማሳካት አንዱ መንገድ በመሆኑ የሐረሪ ክልል መንግስት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሂ በበኩላቸው ድጋፉ የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሰጣጥ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሻሻል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የሁለቱን ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትሥሥር የበለጠ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ድጋፉ የጤና አገልግሎት ጥራትን በማሻሻል ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፤ ለሐረሪ ክልል ህዝብና መንግስት በዞኑ ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ ካሁን በፊት የከሚሴ ሆስፒታል የህክምና ግብአት እጥረት መነሻ በማድረግ ለዞኑ ህዝብ አስፈላጊ ድጋፍ ለማድረግ በተገባው ቃል መሠረት የተደረገ መሆኑ መገለጹን የሐረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል።