Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያና ቻይናን ትብብር የሚያጠናክር ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለውን የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በኮንፍረንሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ፣ ኤስያ እና ፓስፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ንጉሥ ከበደ፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ፣ የጃንግዙ ግዛት የንግድ መምሪያ ዋና ዳይሬክተር ሲ ዮንግ እና የግዛቲቱ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።
አምባሳደር ንጉሥ ከበደ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ያለው የሀገራቱ የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ኢትዮጵያ ከአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን እያደረገች ያለው ጉዞ እውን እንዲሆን የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የቻይናዋ ጃንግዙ ግዛት በዚህ የትብብር ሂደት አይተኬ ሚና እንዳላትም ገልፀዋል።
የግዛቲቱ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ የኢኮኖሚና የንግድ ትብብርን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠዋል።
የኢትዮ-ቻይና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት በኢኮኖሚና ንግድ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የቻይና ጃንግዙ ግዛት የንግድ መምሪያ ዋና ዳይሬክተር ሲ ዮንግ ኢትዮጵያ ለግዛቲቱ ባለሃብቶች ምቹ መዳረሻ እንደሆነች ገልጸዋል።
በተለይ የግዛቲቷ ባለሀብቶች በማኑፋክቸሪንግ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
Exit mobile version