አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የዑጋንዳ አቻውን በመለያ ምት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ዙር ማለፉን አረጋግጧል፡፡
ሉሲዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በካምፓላ ባደረጉበት ወቅት 2 ለ 0 መሸነፋቸው ይታወሳል፡፡
ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው የመልስ ጨዋታ፤ ሉሲዎቹ አረጋሽ ካልሳ እና እፀገነት ግርማ ባስቆጠሯቸው ጎሎች መደበኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2 ለ 0 ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡
ቡድኖቹ በደርሶ መልስ ውጤት ሁለት አቻ መለያየታቸውን ተከትሎም በተሰጠው መለያ ምት፤ ሉሲዎቹ የዑጋንዳ አቻቸውን በመለያ ምት 5 ለ 4 አሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል፡፡
የጨዋታውን ውጤት ተከትሎም፤ በሁለተኛው ዙር ሉሲዎቹ ከታንዛኒያ ጋር የሚጫዎቱ ይሆናል፡፡
ዛሬ በተደረገው የመልስ ጨዋታ አስቀድመው ከሉሲዎቹ ስብስብ ራሳቸውን ያገለሉት እና የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ተጫዋቾች የነበሩት ብርቱካን ገብረክርስቶስ እና ረሒማ ዘርጋው ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ እና እንዳልካቸው ወዳጄ