የሀገር ውስጥ ዜና

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሶማሊያ ጉብኝት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ፋይዳ አለው – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

By Meseret Awoke

February 27, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሶማሊያ ያደረጉት ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ፋይዳ ያለውና ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሶማሊያ ጉብኝት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ ሀገራቱ ለአንድ ዓመት ያህል ትንሽ ሻክሮ ከነበረ ግንኙነት ወጥተው አዲስ የትብብርና የወዳጅነት ምዕራፍ ላይ እንደደረሱ የሚያሳይ ጉብኝት መደረጉን ጠቁመዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም ከአንካራው ስምምነት ጀምሮ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ወራት በተለያየ ደረጃ ሲደረጉ የነበሩ ግንኙነቶች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር መልክ ያስያዙ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በዚህም ከፍተኛ መሻሻሎች መታየታቸውን ጠቁመዋል።

በኢኮኖሚውና በሌሎች በመሰረተ ልማት ዘርፎችም የሚኖሩ ትብብሮችን አስመልክቶ ውይይት ለማድረግ እና ትብብሩ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጉብኝታቸው ጠቃሚ እንደነበርም ተናግረዋል።

በቀጣይም የሀገራቱ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ እንደሚሄድ አመላካች እንደሆነም ገልጸዋል።

ባለፉት ወራት በመሪዎች ደረጃ ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰው፤ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት በአዲስ አበባ ያደረጉትን ጉብኝትም በአብነት አንስተዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በመሆን በሞቃዲሾ ያደረጉት ጉብኝት በመሪዎች መካከል ያለውን ቅርበት፣ ለግንኙነቱ የሰጡትን ትኩረት እና ያለውን የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ፈቃደኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት እንዲሁም ለቀጣናው የምትሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።

በአድማሱ አራጋው