አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በነጩ ቤተመንግስት ያደረጉት ውይይት ያለስምምነት ተጠናቅቋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች የሩሲያ እና ዩክሬንን ጦርነት በሰላማዊ ውይይት መቋጨት በሚቻልበት ሁኔታ ለመምከርና የማዕድን ስምምነት ለመፈራረም ነበር በነጩ ቤተመንግስት የተገናኙት።
ይሁን እንጂ በሃይለ ቃል የታጀበው የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዘለንስኪ ውይይት ያለመግባባት መጠናቀቁ ነው የተገለጸው።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ፥ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ለሰላም ዝግጁ አይደሉም ብለዋል።
“ዘለንስኪ የሩሲያ -ዩክሬንን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በሚደረገው ጥረት የአሜሪካን ምክረ ሃሳብ የማይቀበሉ ከሆነ በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ለመሆን እንገደዳለን” ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፡፡
ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በነጩ ቤተመንግስት ለአሜሪካ ክብር አልሰጡም ሲሉም አንስተዋል።
ቮሎድሚር ዘለንስኪ ለሰላም ዝግጁ ሲሆኑ ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት መምጣት እንደሚችሉም አመልክተዋል።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፥ ለአሜሪካ መንግስትና ሕዝብ ምስጋና አቅርበዋል።
ዩክሬን ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላምን ትሻለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ ፥ ለዚህም በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።