አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ያጋጠሙንን ፈተናዎች በመሻገር ጠንካራና የበለጸገች ሀገር ለመገንባት የዓድዋ ድልን መጠቀም እንደሚገባ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) ገለጹ፡፡
129ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል” በሚል መሪ ቃል በዓድዋ መታሰቢያ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።
የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ አንድነታችንን በማጠናከርና የገጠሙንን ፈተናዎች በመሻገር ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያና አፍሪካን ለመገንባት መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ዓድዋ የምንዘክረው ታሪክ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የምናወርሰው ታላቅ ሃላፊነት ነው ያሉት ሚኒስትሯ÷ ዓድዋ አፍሪካዊያን ለነፃነት የሚያደርጉትን ንቅናቄ በማቀጣጠል ለድል እንዳበቃቸው ገልጸዋል፡፡
ዛሬም በህብረትና በጀግንነት በመነሳሳት ለሀገራችንና ለአፍሪካ ብልፅግና ለማረጋገጥ መትጋት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡